ትኩረቱን በግብርናው መስክ ላይ በማድረግ ምርትን ከገበሬው በቀጥታ ተቀብሎ ለሸማቹ ህብረተሰብ በቅናሽ ዋጋ ለማቅረብ እየሰራ የሚገኘው ፐርፐዝብላክ ኢትዮጵያ የጀመረው ይህ እንቅስቃሴ በሀገራችን አንድ አንድ ህገወጥ ደላሎች በፈጠሩት የተበላሸ የገበያ ስርዓት ሳቢያ ከዕለት ወደ ዕለት እየናረ የመጣውን የሸቀጦች ዋጋ ለማረጋጋት ትልቅ አቅም እንደሚኖረው ፐርፐዝብላክ ሚዲያ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ ባለሙያዎች ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፕሮፌሰር መንግስቱ ከተማ ተናግረዋል፡፡
ማህበሩ ከሚሰራባቸው የስራ መስኮች ውስጥ ዋነኛው የግብርናን እና ገጠር ልማትን በተመለከት ጥናት ማድረግ መሆኑን የገለፁት ፕሮፌሰር መንግስቱ፤ ኩባንያው በከገበሬው የተቀናጀ ኤክስቴንሽን ፐሮግራም ፕሮጀክቱ ገበሬውን በቴክኖሎጂው በማገዝ ከሚያመርተው ምርት የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል እና የተሻለ ህይወት እንዲኖር ለማድረግ እየሰራ የሚገኘው ሥራ ስኬታማ ይሆናል የሚል ዕምነት አለኝ ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር ከበርካታ ተቋማት ጋር በጋራ ይሰራል ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ ከፐርፐዝብላክ ኢትዮጵያ ጋር የተፈራረሙት የስራ መግባቢያ ስምምነት ሰነደ እንደ ማህበር የግብርናውን መስክ የተመለከቱ የተለያዩ ምርምሮችን በማከናወን ኩባንያው ለሚያካውናቸው ሥራዎች ግብዓትነት እንዲውሉ ማስቻል፣ የግብርናውን መስክ የተመለከተ የተለያዩ ኮንፍረሶችን ለማዘጋጀት እና ለሰራተኞቹም የአቅም ግንባታ ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር እ.አ.አ በ1991 በኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች አማካኝነት መቋቋሙን የገለፁት ፕ/ር መንግስቱ፤ ማህበሩ ስራውን ከማንኛውም መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጫና ገለልተኛ በሆነ መልኩ የሚሰራ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የተቋቋመበት ዓላማም በተለያየ የሙያ መስክ ላይ ለተሰማሩ ተቋማት ባሉበት የሙያ መስክ ጠቃሚ ጥናቶችን ማከናወን እንዲሁም አዳዲስ ሀሳቦች ማፍለቅ የሚችሉ የተለያዩ የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀት ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ለተለያዩ አካላት የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት፣ የሚሰሩ ሥራዎችን ለህትመት በማብቃት ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ማሰራጨት እና በሀገሪቱ ውስጥ የሚሰጠው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ለማስቻል ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶች ጋር በቅርበት መስራትም የማህበሩ አንዱ ሀላፊነት መሆኑንም ነው የገለፁት፡፡
ኢትዮጵያ በጣም ሰፊ እና ትልቅ ሀገር ናት ያሉት ፕ/ር መንግስቱ ፐርፐዝብላክ ኢትዮጵያ ብቻውን በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የዋጋ ግሽበት የማረጋጋት አቅም ስለማይኖረው ተመሳሳይ ዓላማን ያነገቡ ተቋማት ሊበራከቱ ይገባል ብለዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ናታን ታደለ

Leave a Reply